Sidama Liberation Front

header hb
.

ከሲዳማ ኤጄቶ በወቅታዊ የሃገራችን ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ሀገራችን ላለፉት 27 ዓመታት እጅግ ክፉ በሆነ ፋሽስታዊና የሕዝብ ድምፅ መስማት በማይፈልግ መንግሥት ስትገዛ ቆይታለች። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የሀገራችንን ሁኔት ስንመለከት ሀገራችን መንግሥት አልባ ከመሆኗም በላይ ሁኔታዉ እጅግ እየከፋና ዜጎች በሠላም ወጥተዉና ሠርተዉ መግባት ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሷል ። የመከላከያ ሠራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበር ከመጠበቅ ይልቅ የትግራይን የበላይነት የማስጠበቅ ሥራ ላይ ተሠማርቷል። ይህንን እኩይ የህወሃትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ለሀገርቷ የሚበጅ አስመስለዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅና ሀገርቷን ወደ ወታደራዊ አገዛዝ በመቀየር ሠላማዊና ንጹሓን ዜጎችን ያለርህራሄ የመግደልና የማፈናቀል ዘመቻ ተያይዘዋል። የሥርዓቱ መሪወችና የሠራዊቱ አዛዦች በግልና በቡድን ሆነዉ የሀገርቱን ሀብት የማራቆትና ወደ ዉጭ የማሸሽ ሥራ ላይ ተጠምደዋል። ድሀዉን አርሶ አደር ያለርህራሄ ከመሬቱ እያፈናቀሉ የመሬት ወረራን ያጧጡፋሉ። ሙሉ በሙሉ በህወሃት ሰዎች ከሚመሩት ከመከላከያና ከደህንነቱ በተጨማሪ በየክልሉ ያሉ በህወሃት ተጠፍጥፈዉ የተሠሩ አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ተጠርነታቸዉ ለህወሃት ስለሆነ ለሚወክሉት ህዝብ የመኖር ፋይዳቸዉ ከጥቅም ይልቅ ጉዳቱ የከፋ ነዉ።

ስለሆነም የሲዳማ ሕዝብ ላለፉት 27 ዓመታት ይህንን ጭቆና አጥብቆ በመቃወም ታግሏል፣ብዙ መስዋዕትም ከፍሏል። የሲዳማ ኤጄቶወችም የሲዳማን ህዝብ ትግል ከዳር ለማድረስ ከህዝቡ ጎን በመቆም ታርካዊ ግዴታቸዉን በመወጣት ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ የትግሉን አድማስ በማስፋትና ከሌሎች ከተጨቆኑ ኢትዮጵያዉያን ወገኖች ጋር በመሆን በተጠከረ ሁኔታ በመታገል ላይ ሲሆን፣አሁን የደረስንበትን ወቅት አሳሳብ ሁኔታ በተመለከተ የሚከተለዉን የአቋም መግለጫ አዉጥቷል።

1. በሀገራችን ያለምንም በቂ ምክንያት የታወጀዉንና የህዝባችንን በሕይወት የመኖርና በሠላም ወጥቶ የመግባት መብታቸዉን ሙሉ በሙሉ የሚጥሰዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጥብቀን እንቃወማለን፤ በአስቸኳይም እንድነሳ እንጠይቃለን።
2. በመከላከያ ሠራዊት በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ የሚደረገዉ ግድያና የማፈናቀል ሥራ በስፋት ቀጥሏል። በተለይም በቅርቡ በአስቸኳይ ጊዜ በተቋቋመዉ ኮማንድ ፖስት ትዕዛዝ በሞያሌ ከተማ የዕለት ተዕለት ተግባራቸዉን እያከናወኑ ባሉ ሠላማዊ ዜጎቻችን ላይ ታቅዶና ታስቦ የተፈፀመዉ ግድያና የማፈናቀል ሥራ የሥርዓቱን አስከፍ ገፅታ አጉልቶ ያሳየ ከመሆኑም በላይ ይህ ሥርዓት ሳይዉል ሳያድር መወገድ እንዳለበት ከመቸዉም ጊዜ በላይ ግልጽ የሆነበት ነዉ። የሲዳማ ኤጄቶወች በሠላማዊ ወገኖቻን ላይ የሚደረጉ ግድያወችንና የማፈናቀል ተግባራትን አጥብቀን እንቃወማለን፤ እናወግዛለንም። ይህንን ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈፅሙ ወንጀለኞችን በአስቸኳይ ለፍርድ ለማቅረብ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ጋር ሆነን በአንድነት እንታገላለን።
3. በደህንነትና በልማት እጦት የተጎዱትን በዓሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የሲዳማ አርሶ አደሮች ላይ የሃዋሳ ከተማ ማስፋፋት በሚል ሰበብ የተጀመረዉን የማፈናቀልና የተለመደዉን የመሬት ወረራ በአስቸኳይ እንድቆም እንጠይቃለን። በተጨማሪም በሃዋሳና በአካባቢዉ ላለፉት 27 ዓመታት ለዘመናት ከኖሩበት ቄዬአቸው እየተፈናቀሉ ለድህነትና ለጎዳና ኑሮ የተዳረጉ የሲዳማ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸዉ በአስቸኳይ ካሳ ተከፍሏቸዉ እንድቋቋሙ እንድደረግ አጥብቀን እንጠይቃለን።
4. ወያኔ ሀርነት ትግራይ በህገወጥ መንገድ ከ57 በላይ ብሄር ብሄረሰቦችን ደቡብ በሚለዉ ቅርጫት ዉስጥ ካጎሬ በኋላ ደኢህዴን የተባለዉን ድርጅት አቋቁሞ ህዝቡን ስጨቁንና ስበዘብዝ መኖሩ ሃቅ ነው። ይህ ድርጅት ማናቸዉንም የደቡብ ብሄር የማይወክል ከመሆኑም በላይ አቅመቢስ የሆነና ከወያኔ ሀርኔት ትግራይ ትእዛዝ እየተቀበለ ለእነርሱ ብቻ የሚሠራ ስለሆነ በአስችኳይ ፈርሶ ህዝቡ ይበጀኛል እና ያስተዳድረኛል የሚለዉን ሥርዓት በነጻነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥ እንድችል በአስቸኳይ እንድደረግ እንጠይቃለን።
5. አስተሳሰባቸዉ ለአገራቸዉና ለህዝባቸዉ ደህንነት እና ዕድገት በመሆኑና ከጨቋኙ ከኢህአዴግ የተለየ በመሆኑ በእሥር ቤቶች የሚሠቃዩ ወገኖቻችን ለጉዳታቸዉ ካሳ ተከፍሏቸዉ በአስቸኳይና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድፈቱ እንጠይቃለን።
6. በመንግሥት ሥራም ሆነ በተለያዩ የፖለቲካ ተቋማት ዉስጥ የተሠማራችሁ የሲዳማ ተወላጆች ከኤጄቶዎች ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ ከጨቋኝ ሥርዓት ሕዝባችንን የመታደግ ታርካዊ አደራችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
7. ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ብቁ አለመሆኑ በተደጋጋም ስለተረጋገጠ በአስቸኳይ የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ ሁሉም ዜጎች የሚሳተፉበት በሕዝብ የተመረጠና ለሕዝብ የሚሠራ መንግሥት የሚመሠረትበት ሁኔታወች እንድመቻቹ እንጠይቃለን።

በሕዝብ ትብብር ጨቋኙና አረመኔ የአንድ ብሄር የሆነ አምባገነን የኢህአዴግ ድርጅት ሥርዓት ይወገዳል!
ኤጄቶ
መጋብት 4 ቀን 2010
ሃዋሳ